የሀላፊ መልእክት
የሲዳማ ብ/ክ/መ/ስ/ክ/ኢ/ል/ቢሮ እንደ ቢሮ የተቋቋመው በ2014 ዓ.ም ሲሆን ሶስት ዋና ዋና ዘርፎችን ማለትም የሙያ ስልጠና እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ዘርፍን፣ የስራ እድል ፈጠራ ዘርፍን እና አሰሪና ሰራተኛ ልማት ዘርፍን አካቶ በመያዝ ለክልሉ ብሎም ለሀገር አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቶአል፡፡
አሰሪና ሰራተኛ ልማት ዘርፍ ከስራ፣ ከሰራተኛ ገበያ መረጃ፣ ከኢንዱስትሪ ግንኙነት እንዲሁም ከስራ ደህንነትና ከጤና ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ሃላፊነትን ወስዶ ይሰራል።በአሰሪና በሰራተኞች መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲሁም በአሰሪ፣ በሠራተኛና በመንግሥት መካከል ያለውን የሦስትዮሽ ግንኙነትን የማጠናከር ተግባራትን ያከናውናል፡፡ የግሉ ሴክተር የአሰሪና የሠራተኛ ግንኙነት ለመምራት የወጡ ፖሊሲዎች እና የሕግ ማዕቀፎች በክልሉ ተግባራዊ መሆናቸውን በበላይነት ይከታተላል፡፡
ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ለአንድ ሀገር ክህሎት፣መልካም አመለካከት እና እውቀት ያላቸውን ወጣቶች የማፍራት ዓላማ ያለው የትምህርት ስርዓት አካል ነው። ኢትዮጵያን ጨምሮ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት TVETን ለኢኮኖሚ ዕድገትና ሥራ አጥነትን ለመቀነስ ዋና መሳሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡ በቢሮው የሚገኘው የሙያ ስልጠና እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ዘርፍ በክልሉ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን የሚያግዙ መሰረታዊ መለስተኛና መካከለኛ ደረጃ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማትን ያቋቁማል፣ ያስፋፋል፣ይደግፋል፣ ያስተዳድራል፡፡
የስራ እድል ፈጠራ ዘርፍ ለክልሉ ሥራ ፈላጊዎች በተለይም ለወጣቶች እና ለሴቶች በስራ ፈጠራ ላይ በስፋት እንዲሰማሩ የስልጠና ድጋፍ፣ መስሪያ ቦታ፣ ብድር፣ ገበያ ትስስር ምክር እና ሌሎች ድጋፎች እንዲያገኙ ያደርጋል፣ ያመቻቻል፡፡